top of page
Search

45ኛው የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም (KAIF)/ከምባቶማ ኢንተርናሽናል ፎረም (KIF) ስብሰባ ቅዳሜ ሜይ 1ቀን 2021 ተካሂዷል።

Writer's picture: kambattomaikambattomai

የውይይቱ ርዕስ በሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ/አስተውሎት ወይም በArtificial Intelligence ላይ ያተኮረ ነበር። የውይይቱ አዘጋጅና አቅራቢ የከምባቶማ ኢንተርናሽናል አክሽን ፎረም አባል የሆኑት

ዕጩ ዶክተር ሰላሙ ይስሃቅ ሐንዲሶ ነበሩ።

ዕጩ ዶ/ር ሰላሙ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ካገኙ በኋላ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ከኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በሥራ ዓለም በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ከባለሙያነት አንስተዉ በተለያዩ የመንግስት ሃላፊነት ሥፍራዎችም አገልግለዋል። ባሁኑ ወቅት የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ትምህርታቸውን በቻይና ሀገር በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙና በሚማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወደ 17 ጥናታዊ ጽሁፎችን ያሳተሙ ናቸው።

የዛሬውን ውይይት ያቀረቡት በሁለት ክፍሎች በመመደብ ነበር። ክፍል አንድን የጀመሩት አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ምንድን ነው? በሚል ጥያቄ ነበር። በመቀጠልም ስለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፍልስፍና፤ አጀማመርና ዕድገት ታሪክ፤ ዓላማው፤አስተዋጾ፤ ቴክኒክ፤ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አፕሊኬሽን ዓይነቶች፤ ጠቀሜታዎች እና የወደፊት አቅጣጫዎች በslides የተደገፈ መግላጫዎችንና ትንታኔዎችን ሰጥተዋል።


በክፍል ሁለት በማምረቻ/ማፈብረኪያ (manufacturing) እና የኢንዱስትሪ ሮቦቶች ዘርፍ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቁልፍ ቴክኖሎጂ ስላለውና ስለሚኖረው ሚና አብራርተዋል። ባሁኑ ጊዜ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አለምን dominate ለማድረግ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ስለሚገኙ ሀገሮች ገለጻ ተሰጥቷል።

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ሥራ ላይ ለማዋል በሁለት ማዕከላት በተለይም በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተመርቆ ስለተከፈው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረት ያደረገ ሉባን ወርክሾፕ ማዕክል በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። ዶ/ር ሰላሙ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ሲመልሱ የሚሰሩት በዚሁ ማዕከል ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም እሳቸውም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት የበኩላቸውን አስተዋዕጾ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።

ጥቄዎች ቀርበው መልሰዋል። የኢንተለጀንስ የጅማሮ ሥራዎች በከምባታ ጠምባሮ ዞን ከአሁኑ መሰራት እንደሚኖርባቸው እና የከምባታ ጠምባሮ ዞን ተማሪዎች ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ከመሄዳቸው በፊት ከኮምፒውተር (I.C.T) ጋር ተዋውቀው መሄድ እንደሚኖርባቸው፤ ቢያንስ በየወረዳው ወይም በየከተማው የኮምፒዩተር(I.C.T) ማዕከል መቋቋም እንደሚኖርበት፤ ለዚህም ተግባራዊነት የከምባታ ጠምባሮ ልማት ማህበር (ጎጎታ ኬር) እና የዞኑ አስተዳደር በግንባር ቀደምትነት መሥራት እንደሚኖርባቸው አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። ከቤቱም ገንቢ ሀሳቦች ተሰጥተው ተገቢ ግንዛቤ ተገኝቷል።ከረጂ ድርጅቶች (NGO's) ሀብት (ገንዘብ) በማፈላለግ ረገድ፤ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች እንዲሁም ወዳጆች በግልም ሆነ በቡድን የማንቀሳቀስ አስፈላጊነት እና በዚህም ረገድ የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም (K.A.I.F) የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ተጠቅሶ በእለቱ በርዕሱ ዙሪያ ላይ ሲደረግ የነበረው ውይይት ተጠቃሏል።

ወደፊት የሚደረጉ ስብሰባዎች ከመጀመራቸው በፊት ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃ ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ትንሽ ገለጻ የሚደረግ ቢሆን የሚል አስተያየት ከተሳታፊዎች ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል።በዚህም መሠረት ወደፊት የሚደረጉ ስብሰባዎች ከመጀመራቸው በፊት ጠቅለል ያለ ገለጻ ለጥቂት ደቂቃዎች እንደሚሰጥ በሰብሳቢው በኩል ተገልጿል። በዚሁም የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቅቋል።






ኡጀቀንቹኔ ምናደብሃት።

ሜጦመት መቆሃ! ሰላም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ይሁን







5 views0 comments

コメント


Post: Blog2_Post
bottom of page