top of page
Search

KAIF - KMG Ethiopia Partnership

  • Writer: kambattomai
    kambattomai
  • 11 hours ago
  • 4 min read

ለዉድ ወገኖቻችንና ደጋፊዎቻችን በሙሉ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም.

የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም (Kambattoma Action International Forum/KAIF) ከ KMG Ethiopia ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችለዉን የጋራ መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of Understanding/MoU) ባለፈዉ February 2025 ተፈራርሞ በጋራ መንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መሆኑን ስንገልፅ በደስታ ነዉ።


የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም በአሜሪካ ሀገር ሕጋዊ ፈቃድ ያለውና የተመዘገበ የሕዝብንና የአካባቢን ልማት ከማሳደግ አንጻር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ፤ ምንጊዜም ለከምባታ ሕዝብ እድገት፣ ልማትና አንድነት የሚሰራ የበጎ አድራጊ ድርጅት ነው። በተለይም ለትምህርት፣ለባህልና ለሲቪክ መስኮች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገና ከጅምሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ደንግጎ የተነሳና እስከዛሬ ድረስ በሚችለው ሁሉ ተግባራዊ እያደረገ የቀጠለ ሕዝብን፣ አካባቢውን የሚያስቀድም ወገን ረጂ ድርጅት ነው፡፡

ከምባታን የሚመለከቱ አንገብጋቢ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ድርጅታችን ፈጥኖ የሚደርስና በውጭ ሀገራት ነዋሪ የሆኑ የከምባታ ተወላጆችን በመድረስ ለወገን ደራሽ በመሆን ከሕዝባችን ጎን እንዲቆሙ ላቅ ያለ ሚና ሲጫወት የቆየ መንግሥታዊ ያልሆነ በግልጽና በዕውቅ እየሰራ ያለ ድርጅት ነው። ድርጅታችን ህግንና መመሪያን መሰረት አድርጎ የሚሰራ፤ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ተወላጆቻችን፣ ወዳጆቻችንና ደጋፊዎቻችን የለገሱትና የሚለግሱት ገንዘብ በቀጥታ በድርጅታችን ሕጋዊ የባንክ አካውንት የሚገባ፤ በባለሙያ ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት ከአደራረግ እስከ አፈጻጸም ሕጋዊነትን መሰረት አድርጎ ለተመሰረተበት ኣላማ በቁርጠኝነትና በታማኝነት የሰራና አሁንም እየሰራ የሚገኝ ለውጥ ተኮር ድርጅት ነው፡፡


እስካሁን ካደረግናቸው ክንውኖች መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል፦

  1.  ከፋ ዉስጥ በሚኖሩ የከምባታ ተወላጆች ላይ ጥቃትና የማፈናቀል አደጋ በደረሰበት ወቅት በዓላም ላይ የሚገኙ የከምባታን ዲያስፖራ በማንቀሳቀስ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉና ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ለጊዜያዊና ዘላቂ እርዳታ የሚሆን $37,000.00 ዶላር በመሰብሰብ በከምባታ ዞን መንግስት በኩል ለተጎዱ ወገኖቻችን አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እንዲደርስ አድርጓል።

  2.  የአሁኑ የከምባታ ልማት ድርጅት(የቀድሞዉ የጎጎታ ኬር) የተመሰረተበትን 25ኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ ሲያከብር ለልማት ድርጅቱ ያለንን አድናቆት ለማሳየት አሜሪካ ሀገር ከሚኖሩ የዞናችን ተወላጆች የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበናል። ከድርጅታችን የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ትምህርት በመሆኑ የተዋጠው ገንዘብ ለዞኑ ት/ቤቶች ቢውል የሚል ሃሳብ ለጎጎታ ኬር አመራር አቅርበን ከመስማማታቸውም በላይ እርዳታው በምን መልኩ ቢሆን ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ጭምር አጥንተው ባቀረቡት መሰረት ለ8 የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች [ጆሬ፤ ጉልባና፤ ሆዶ፤ ሠረራ፤ ፋንዲዴ፤ አመለቃና ሆላገባ ዛቶ ት/ቤቶች] ከ220,000 ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ900 መቶ በላይ ማጣቀሻ መጽሃፍት (reference books) ተገዝተው እንዲሰጡ አድርጓል። እንዲሁም ለቃጫ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት 112 የቤት ኪዳን ቆርቆሮ ተገዝቶ ተሰጥቷል።

  3. ማስተር አብነት ከበደ የሞተር ብስክሌት ትርዒት በሚያሳይበት ወቅት ይጠቀምበት የነበረው ሞተር ብስክሌት ያረጀ በመሆኑና እሱም የከምባታን ስም ይዞ ባህላችንንና ወጋችንንም ከማሳየትና ከማጉላትም አንጻር ሲጫወት የነበረውን ወገተኝነትን ግምት ውስጥ በማስገባት እየሰራና እያስጠራ የነበረው ከምባታንና መላው አካባቢውንና ሀገርንም ስለነበር፤ አቅምና ችሎታም የነበረው ወጣት መሆኑን በመገንዘብ የድርጅታችን አባላት በግል ተነሳሽነት ፈቃደኛ ለሆኑ የዞኑ ተወላጆች የድጋፍ ጥሪ አቅርበው $1,855.00 የአሜሪካን ዶላር ተለግሷል። ከዚህ ውስጥ የጎፈንድ ድርጅት $58.90 የአገልግሎት ክፍያ ቆርጦ ከቀረው $1796.10 ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ሲላክ $26.54 የትራንስፈር ክፍያ ተክፍሎ የቀረው $1,769.56 ለማስተር አብነት ተልኮ ደርሶታል። ሌሎች ሁለት ወገኖች በኢትዮጵያ ባንክ አካውንት ለዚሁ አላማ 9,000.00 ብር አስገብተውለታል። በተዋጠው ገንዘብ ማስተር አብነት ሌለ የተሻለች ሞተር ብስክሌት እንዲገዛ ወገናዊና ወቅታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አሁን ያለበትንና የሚፈጽማቸውን የወገንተኝነትንና የሰብዓዊ ሥራዎችን ሲሰራ ስናይ በውጤቱ ደስ ብሎን እግዚአብሄርን እናመሰግናለን።

  4.  የሂጋ ልዩ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የበጀት እጥረት አጋጥሞት ለዞኑ ተወላጆች የገንዘብ ድጋፍ ጥሪ በተደረገበት ወቅት ከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም አሜሪካ ሀገር ከሚገኙ የከምባታ ተወላጆችና ከአባላቱ 321,100.00 ብር ሰብስቦ በመላክ ት/ቤቱን ከዉድቀት ለማዳን የተደረገው እንቅስቃሴ አካል በመሆን ተገቢውን የአለኝታነቱን ሚና ተጫውቷል።

  5.  ድርጅታችን በርካታ የዉይይት መድረኮችን አዘጋጅቶ የተለያዩ የከምባታ ምሁራንን ወደ ፎረሙ ጋብዞ ብዙዎች የህይወት፣ የሥራ፣ የሙያና የእዉቀት ልምዳቸዉን እንዲያካፍሉ ሲያደርግ ቆይቷል። በከምባታ ልማት፤ እድገትና አንድነት ጉዳዮች ዙሪያ በማወያየት ጠቃሚ ሃሳቦችን፤ የወደፊት አቅጣጫዎችን፣ ትልሞችንና አስተያየቶችን አሰባስቧል። ይህንኑ ወደፊትም ይቀጥላል።

 ከእነዚህ ተጋባዥ እንግዶቻችን መካከል አንዱ አቶ ኃይሌ ዳንኤል ማጊቾ ናቸዉ። በዉይይቱ ወቅት አቶ ኃይሌ የከምባታን ባህልና ታሪክ የሚገልፅ መፅሃፍ ጽፈዉ ለማሳተም የገንዘብ አቅም እንደሌላቸውና የፃፉትንም ጽሁፍ እቤት ለማስቀመጥ መገደዳቸዉን በመግለፃቸዉ የድርጅታችን አመራር ቦርድ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ የከምባታን ባህልና ታሪክ የሚያጎሉ ጉዳዮችን መደገፍ ከመርሆዎቻችን አንዱ ስለሆነ የአቶ ኃይሌን መፅሃፍ ለማሳተም የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ ወሰነ። በዚሁ መሰረት ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን በማድረግ የfund፟raising ጥሪ ለዞናችን ተወላጆች አድርገን አሜሪካ ከሚገኙ የዞኑ ተወላጆች 320,544.00 ብር፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው የአቶ ኃይሌ አካውንት ደግሞ በኢትዮጵያና ሌሎች ሀገሮች ከሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች 301,000.00 በድምሩ 621,544.00 ተዋጥቶ ለአቶ ኃይሌ ዳንኤል ማጊቾ እንዲደርስ ተደርጓል።

  1. የሐምባርቾ የወንዶችና ሴቶች የእግር ኳስ ቡድኖች ወደ ፕሪመርሊግ ባለፉበት ወቅት ለሁለቱም ቡድኖች አቀባበል እንዲረዳ 105,600.00 ብር ዞኑ በከፈተው የቡድኑ አካውንት ገቢ በማድረግ የአቀባባሉና የደስታው ተካፋይ ሆነናል።

  2. ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በገንዘብ የሚተመኑና የማይተመኑ በርካታ ጉዳዮችን ሲያከናውን የቆየ ድርጅት ነው።


KMG ETHIOPIA ዶ/ር ቦጋለች ገብሬ ለሕዝባቸው እድገት፤ ልማት፤ ለሴቶችና ልጃገረዶች እኩልነት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት በነበራቸው ራዕይና አርቆ አሳቢነት እአአ በ1997 የተመሰረተና በኢትዮጵያ ሲቪክ ሶሳይቲ ኤጀንሲ ሀገራዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ፤ ከከምባታ አልፎ በሌሎች ዞኖች ጭምር ድንቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶችን ያስመዘገበ ሀገራዊ ስመጥር ድርጅት ነው። በዶ/ር ቦጋለች ትጉህነት፤ ታታሪነትና ያላሰለሰ ጥረት የልጃገረዶች ግርዛት ሙሉ በሙሉ እስከ መጥፋት ደርሶ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የልጃገረዶችን ግርዛት በማስቆም ረገድ የተገኘው ውጤት በተለይ ከዶ/ር ቦጋለች ህልፈት በኋላ ጎጂ ባህሉ በመጥፋት አፋፍ ላይ ከነበረበት ተመልሶ እየተስፋፋ መሆኑን መስማት ሁላችንንም የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን ቁጭት የሚያሳድርም ነው።

የ KAIF-KMG ETHIOPIA MoU ሁለቱን እህት ድርጅቶች የበለጠ የሚያቀራረብ፤ የእውቀት የልምድና የሪሶርስ ልውውጥን የሚያሳልጥ፤ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በጋራ ለመቅረጽና ሀብት/ገንዘብ ለማፈላልግ የሚያስችል፤ እንዲሁም ከእርስ በርስ ለመማማር፤ አብሮ ለማቀድና ለመተግበር የሚያስችል ጥምረት እንደሚሆን ሁለቱም ድርጅቶች ያምናሉ።

አሁን በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት የግርዘት ጎጂ ባህል እንዳያንሰራራ የሕብረተ ሰብ ተደራሽነትን የሚያጎለብት፤ በውጭና በውስጥ ያሉ የከምባታ ተወላጆች በዞኑ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳርፉ የሚገፋፋ በጥቅሉ የዶ/ር ቦጋለችን ራዕይ የሚያስቀጥል እንደሚሆን እንተማመናለን።


በሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች ማለትም ከምባቶማ አክሽን ኢንቴርናሽናል ፎረም (KAIF) እና ኬኤምጂ (KMG) የተደረገው የመግባቢያና አብሮ የመሥራት ሰነድ ፊርማ ለKMG ቀጣይነት፣ ለሕዝባችን ተጠቃሚነትና ለጋራ ራዕያችን ተፈጻሚነት፤ ለስኬታማ ክንውንና አፈጻጻም እንዲሁም ኬኤምጂ የተመሰረተበትንና የተቋቋመበትን ዓላማ እውን እየሆነ እንዲቀጥል የሚያደርግ ስምምነት መሆኑን ለድርጅታችን አባላት፣ ለወዳጆቻችን፣ ለደጋፊዎቻችን፣ ለከምባታ ማኅበረሰባችን ስናሳውቅ በታላቅ ደስታና በአክብሮት ነው፡፡

የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም ቦርድ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም.



 
 
 

Comentários


Post: Blog2_Post
bottom of page