ካለፉት በርካታ ወራት አንሥቶ ለማስተር አብነት ከበደ ሞተር ብስክሌት መግዣ ገንዘብ ከበጎ አድራጊ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ተወላጆች ስናሰባሰብ ቆይተን ገንዘቡን በቅርቡ ለእርሱ ማስተላለፋችንን መግለፃችን ይታወሳል። ያንን ገንዘብ በመጠቀም በትናንትናው ዕለት ሕዳር 9 ቀን 2021 ዓ.ም. (ኖቬምበር 19, 2021) ማስተማር አብነት ሞተር ብስክሌቱን ታዛቢዎች በተገኙበት በሕጋዊ ሰነድ ተፈራርሞ ገዝቷል።
ለተደረገለት እርዳታ ልባዊ ምሥጋናዉን በመግለፅ የግዢዉን ዉል ሙሉ ሰነድ ጭምር አሳውቆናል።
ለማስተር አብነት ሞተር ብስክሌት መግዣ ገንዘብ ለመሰብሰብ የተነሳሱ ግለሰቦች በሶሻል ሚዲያ ካልሆነ በስተቀር አንዳቸውም እሱን በአካል አያውቁትም። እሱም አያውቃቸውም። ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀመርም ሆነ በጎፈንድሚ አካውንት ሲከፈት ማስተር አብነት አላወቀም። ያወቀው ከዚያ በኋላ ነበር። ገና ከመነሻው የማይተዋወቁ ሰዎች ለማያዉቁት ሰው በጎ ነገር ለማድረግ የተነሳሱበትና ያንን በጎነት በተግባር የተረጎሙበት ለብዙዎች አርአያ ሊሆን የሚችል ሥራ ነው።
በአሜሪካና በተለያዩ ሀገሮች የምትኖሩ ለሞተር ብስክሌቱ መግዣ መዋጮ ያደረጋችሁት የከምባታ ጠምባሮ ዞን ተወላጆች እንዲሁም የአሰባሰቡን ሒደት በማስተባበር እና ከተሰበሰበው ገንዘብ አንዳች ሳንቲም ሳይጎድል በሕጋዊ መንገድ ለማስተር አብነት እንዲተላለፍ ላደረጉት የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም አባላትና አመራር ልባዊ ምሥጋናችንን እናቀርባለን።
ማስተር አብነት በተደረገለት በጎነት ደስተኛ ነው። በአሁኑ ሰዓት ሞተሯን በመጠቀም ላይ ይገኛል። ገንዘብ ያዋጣችሁ ወገኖች ለደስታዉ ምክንያት ስለሆናችሁ እናንተም ደስ ይበላችሁ እንላለን። ኖቬምበር 20, 2021።
Comments