top of page
Search

በደቡብ አፍሪካ እና በመላው ዓለም የምትገኙ የከምባታ ተወላጆና ወዳጆች እንኳን ደስ አላችሁ።

Writer's picture: kambattomaikambattomai

ከሁሉ በፊት በአንድ ልብ፣ በአንድ ዓላማ፣ በአንድ ድምጽና በአንድ አይነት መነሳሳት ሕዝባችንንና አካባቢያችንን በልማት ለማገዝ ወስናችሁ “የከምባታ ልማት ማኅበር” በመመስረታችሁ የተሰማኝን ደስታ በራሴና በከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም ስም ስገልጽ በእናንተ በሀገሬ ልጆች ከፍተኛ ኩራት እየተሰማኝ ነው። ይህን ሕብረት ለመፍጠር የተለያዩ ተግዳሮቶችንና ቋጠሮዎችን አልፋችሁ አሁን የደረሳችሁት ርቀት፤ የገነባችሁት ጠንካራ አንድነት፤ ያነገባችሁት ራዕይ፣ ያላችሁ አቅምና ጉልበት እንዲሁም ያዳበራችሁት መግባባትና መከባበር ሕዝባችንንና አካባቢያችን ከመጥቀም አልፎ ለሁላችንም አርአያ ሆኖ ሲጠቀስ የሚኖር ነው።

ትናንትናን ወደኋላ ትተን ዛሬን በመኖር ለነገ ማቀድና መተንበይ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በቁጭትና በቁርጠኝነት ተነሳስታችሁ ዛሬ ደርባን ከተማ "የከምባታ ልማት ማህበር" በመመስረታችሁ ደስታችን የላቀ ነው። የመሰረታችሁት “የከምባታ ልማት ማኅበር” ስያሜው፣ አደረጃጀቱና ዓላማውም አንድ ወጥ በመሆኑ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ፤ አቃፊ፣ አሳታፊ፣ አሳዳጊ፤ የማኅበረሰባችንን ኑሮ የሚያሻሽልና የሚለውጥ እንደሚሆን ጽኑ እምነታችን ነው። በአንድነት ውስጥ ያለውን ጉልበትና ምስጢር የሚያውቁ የልማትና የዕድገት ፀሮች አንድ ሆነን ለሕዝባችን፣ ለአካባቢያችንንና ለሀገራችንም ልማት ቀናውንና መልካሙን እንዳናስብና እንዳናደርግ እንቅፋትና መሰናካያ እየፈጠሩ መንገዶቻችንን በመዝጋት ጉዞአችንን እስከ ማገድ ደርሰው የነበረ ቢሆንም፤ የፈጣሪ ቃል ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚል የእናንተ በአንድነት መነሳሳት የተቀሩትንም የከምባታ ተወላጆች በየአሉበት የሚያነሳሳ እና ለምንመኘው የከምባታ አንድነት ትንሳኤ እንደሚሆን እናምናለን።

የእናንተ መደራጀት፤ በአንድ ዓላማና አመራር ሥር መሆን እኛ በከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም ከዚህ በፊት በከምባታ ዞን ውስጥ ልንሰራ በተለምናቸውና ስንሰራ በነበሩት በትምሀርት፣ በጤናና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንችለውን ሁሉ በአንድ ልብ፣ በአንድ ዓላማና በጋራ ራዕይ ለሕዝባችን፣ ለአካባቢያችንና ለሀገራችን በቀናነትና በመልካምነት አብረን ለመስራት የሚያነሳሳ በመሆኑ በጋራ የምንጫወተው ሚና ቀላል እንደማይሆን እናምናለን። በመሆኑም አቅማችንንና ጉልበታችንን አስተባብረን በሕዝባችን መካከል ገብተን ምኞታችንንና ራዕያችንን ወደ ተግባር እንደምንለውጥ እንተማመናለን።

እኛም የከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም አባላት፤ ወዳጆች፤ ደጋፊዎችና መሪዎች በደቡብ አፍሪካ ለተመሰረተው ለከምባታ ልማት ማኅበር ሥራ አመራሮች፣ አባሎችና ለመላው የማኅበረሰባችን ተወላጆች በተለይም የአንድነትን ጥቅምና ዋጋ በማወቅና በመረዳት እስካዛሬ ለመሩአችሁ፣ ላሰባሰቡአችሁና የመፍትሄ ሃሳቦችንና መንገዶቹንም ላሳዩአችሁ ቆራጥ፣ አስተዋይና አደራጅ ወንድሞች፤ እህቶችና ወገኖች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን አድናቆታችንንና አክብሮታችንን እንገልጻለን። እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን!! አንድነታችን ይጠንክር!

ካሣ ደንታሞ የከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም ፕሬዚደንት ከአሜሪካ

5 views0 comments

Comentários


Post: Blog2_Post
bottom of page