top of page
Search

#ከምባቶማ_አክሽን_አለምአቀፍ_ፎረም:-

Writer's picture: kambattomaikambattomai

በአካባቢያችን የሆነው፣ እየሆነ ያለውና ነገም ሊሆኑ ይችላሉ ብለን የምንሰጋባቸው ጉዳዮች እንደ ገመድ የተገማመዱና የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ በቤተሰብ፣ በጎጥ፣ በመንደር፣ በቀበሌ፣ በአካባቢ፣ በወረዳ፣ በልዩ ወረዳ፣ በዞን፣ ክልል በተባለው፣ በሀገርና በሕዝብ ጫንቃ ላይ ሆን ተብሎ ከወያኔ ገዥ መደብ (ጁንታ) በኩል በደንብ ታስቦና ታቅዶ የተዘረጋ የኅሊውና ማስጠበቂያና ማቆያ የአሰራር መዋቅር ነበር።

ለዘመናት በሰላም አብሮ ሲኖር የነበረውን ማህበረሰብ ከቤተሰብ ጀምሮ አንድ ለአምስት በሚል በስለላ መረብ (ስልት) አዋቅሮ እንኳን ከማህበረሰብ ከባልና ሚስት የየዕለት ዝንባሌአቸውንና ወሬን ሲለቅምና ሲያስለቅም የኖረ በማህበረሰብ ዕድገትና ቅርብርብ እጅግ ክፉና አደገኛ የሚባል የጥርጣሬ መንፈስና ተግባር ያስከተለ ለእኩይ ዓላማው ሌላውንም ማህበረሰብ እየተጠቀመ ሌት ተቀንም እያሰራ እስከ ዕለተ ግባአቱ የሰነበተ ሀገርና ሕዝብ ጠል መንግሥት ነበር።


ብሔርንና ብሔረሰብን ሆን ብሎ በማበጣበጥ እንዲሁም ትናንትም ሆነ ዛሬ ለተጋፈጥነውና እየተጋፈጥን ላለነውም ዘር ተኮር ብጥብጥ፣ መከራና ስቃይ እንድንበቃ በስልትና በጥበብ ለራሳቸው ብቻ በሚጠቅምና በሚመች መንገድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የአስተዳደርም ሆነ የቁጥጥር ዘዴን በመዘርጋት እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ እየተበላላን እንድንኖር በዘረጉት የመበላላትና የመበጣበጥ መስመር ብቻ ሥራዎቻችንን እያከናወንን እንደ ውኃም በተቀደደልን ቦይ ብቻ እየፈሰስን ራሳችንንና ሕዝባችንን እየጎዳን አሁን ላለንበት ጣት መቀሳሰርና መበላላት ደረጃ ደርሰናል።

አውቆ ለወጠነው መሳቂያ፣ ለራሳችን ግን ውርደትና ሀፍረት እየሆነብን በአልባሌና በአጓጉል ተግባሮች ውስጥ ተዘፍቀን በሚያስገምትና በሚያሳፍር ጉዞ ላይ እንገኛለን።

ከሕዝብ አብራክ ወጥተው በወረዳዎችና በዞኑ ሲያስተዳድሩና ሲመሩ የነበሩና አሁንም እየመሩ ያሉ አመራሮች ይብዛም ይነስም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ ብለን እንገምታለን። በእነዚህ ወገኖች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚወሰደው እርምጃ ሕዝቡን ያማከለ ይሁን አይሁን የሚታወቅ ባይሆንም፤ ዛሬ ትክክል አይደለም ተብሎ ጣት ለሚቀሰረው ችግር አመራሩ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም አውቆም ሆነ ሳያውቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የተደረገበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት አለን፣ ወደ ዝርዝር ባይገባም።

ይህ ጊዜውንና ወቅቱን ጠብቆ ከተፍ የሚለው ሹምሽረት ወይም ምርጫ በመጣ ቁጥር የማያንኳኳው በር ባለመኖሩ “የፀሐዩን ሙቀት” ሁሉም እየሞቀው ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ አመራሮች በተመደቡበት ቦታ የአቅማቸውን ሰርተውና አበርክተው ጊዜው ሲደርስ ወይም ለውጥ ሲያስፈልግ ቦታቸውን መልቀቅ ካለባቸው በክብርና በምስጋና ሆኖ የሚያስጠይቃቸው ጉዳይ ካለ በሌላ በኩል እንደ ማንኛውም ዜጋ በሕግ የሚታይ መሆን ይኖርበታል እንጂ ባለተጨበጠና ባልተወሰነ ጉዳይ ላይ ስለሰዎቹ አሉባልታን ማውራትና ማስወራት ትክክለኛ አካሄድ አይመስለንም። ከእኛ መሪ እንዲወጣ የምንፈልግ ከሆነ መሪዎቻችንን ማክበርና ማድመጥ ተገቢ ሲሆን ለሰሩት ፍርደገምድል ጉዳይና ጥፋት በሕጉ መሠረት መጠየቅ አግባብነት ይኖረዋል።

በሌላው በኩል እያገለገሉ ባሉ መሪዎች ላይም ሆነ አገልግለው በሄዱ ላይ ሆን ብሎ አሉባልታን ማውራትና ማስወራት የሥነ-ምግባር ጉድለት ከመሆኑም በላይ ሌሎች በምክንያት የሚነፉትን ጥሩምባ ተቀብለን እኛው፣ በእኛው፣ ለእኛው ባንነፋ ይመረጣል። ምክንያቱም ሌሎች ለምን እንደሚነፉና እንዲነፋላቸውም እንደሚፈልጉ አናውቅምና ነው።

እንደ አንድ ማኅበረሰብና ዞን የሚለማንንና የሚጠቅመንን አስተውለን እንወቅ! ዛሬ የሚዘራውን ነገ የምናጭድ መሆናችንን ካልተገነዘብን ተመልሰን የዚያው ችግር ገፈት ቀማሽ እንሆናለንና ትኩረታችን በመልካም ነገር ላይ ብቻ ይሁን! ፍርደገምድል ሆነን፣ ፍርድን እያዛባን፣ እውነትን እየቀበርን፣ ግራና ቀኙን አይተን ሳናጣራና ሳናመዛዝን በጭፍኑ በወገን ላይ የፈጸምናቸውን ወይም የምንፈጽማቸውን በደል ብናውቅም ባናውቅም በብዙ መልኩ ጎድቶናል። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ወይም ተጠሪዎቻችንን በማናውቀው ጉዳይ ገብተን ከዕድገታቸው ወደኋላ እንዳናስቀር የምናደርገውን ሁሉ በማስተዋል እናድርግ።

ልባችን እያወቀ፣ ኅሊናችን እየወቀሰ፤ ማ ቢወልድ ማ በሚለው ፍልስፍናና ዘመን ባመጣሽ መጠላለፍ ተጠማምደን አካባቢው በልማት እንዳይለማና እንዳያድግ እያደረግን የፍጥነት ሂደቱን እንዳናጓትት መረዳት ይኑረን።

ብቃት፣ችሎታ፣ ልምድ፣ እይታና ራዕይ ያላቸውን ጎበዝ ተፎካካሪዎቻችንን ወያኔ ምክንያት እየፈለገ በግምገማ ተብዬው ተላላኪዎቹን በመጠቀም ከመድረክ ውጭ ያደርግ ነበር። የወቅቱ መንግሥት ይህንን ስህተት አይደግምም ብለን እንገምታለን።

ሀገሪቷ ጀግናና እውነት የሚሰራ ሰው ያስፈልጋታልና በምርጫ ሰበብ የሚሰራው ደባ በሕዝቡና በአካባቢው ዕድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳያስከትል ሰከን ብሎ ማየቱ ተገቢ ይመስለናል።

የዚህ ዓይነት ክፋት፣ ማሳበቅና በራስ ሰው ላይ ተንኮል መስራት ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም አግጦና አፍጥጦ የመጣው የደርግ አባልና በቀድሞው የከምባታና ሐዲያ አውራጃ አስተዳዳሪና የኢሠፓ ዋና ጸሓፊ በነበሩት በጓድ በጴጥሮስ ገብሬ ላይ ሲሆን፤ ተመሳሳይ ሽረባ፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ የዘረኝነት መንፈስ፣ ጠልፎ መጣልና ለራሳችን ሰው መሰናክልና ማናቆ መሆን ደግሞ በክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ሐቢሶ ላይ ዘመቻ መደረጉ ይታወሳል። በተመሳሳይ ሁኔታ እንግልትና መከራ የደረሰባቸው የወገኖቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም።

ከማህበረሰባችን በአቅማቸውም ሆነ ከአቅማቸው በላይ ቤቴን ንብረቴን ሳይሉ ለማህበረሰቡና ለአካባቢው ለውጥ፣ መሻሻልና ዕድገት ሳይታክቱ፣ ደከመኝ፣ ሳለቸኝ ሳይሉ ከገበሬ ማህበር እስከ ወረዳና አውራጃ ድረስ በሊቀመንበርነት ያገለገሉት አባቶችና የወቅቱ የከተማ ካንቲባዎች ወይም የማዘጋጃ ኃላፊዎችም ጭምር የገፈቱ ቀማሾች ሆነው አልፈዋል።

ይህ የመገፋፋትና የመጠላለፍ ሂደት በትንሽ ነገር የማይወዱትን ሰው ወይም እውነተኛ ሆኖ የተገኘን ጎበዝ ሰው ከመስመር የማስወጣት አባዜ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ጎድቶናል። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በአደገኛ ሁኔታ በብዙ መልክ ራሳችንን እየጎዳን፣ ገመናችንን እያጋለጥን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ራሳችንንና ኅብረተሰባችንን እየበደልን ወንድም እህቶቻችንን ደግሞ እርግጠኛ ላልሆንበት፣ ባልገባንና ባልጨበጥነው ጉዳይ ሰለባ እንዲሆኑ በማድረግ በሕይወታቸውም ሆነ በኑሮአቸው ላይ አላስፈላጊ ጥላ ማጥላት የለብንም።

በጊዜአቸው ምንም ይሁን ምን ለሕዝቡና ለአካባቢው በሰሩትና ባበረከቱት መጠን ሚዛናቸው ይለካ፣ ውጤታቸውም ይታይ። ለቀረውና ለጎደለው ማህበረሰቡና አመራሩ እንዴት በአንድነት ለጋራ ስኬት በተቀናጀ መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን መተግበርም እንዳለባቸው ተቀናጅተው ቢሰሩ ተገቢ ነው።

በታቀዱና በታሰቡ ፕሮጄክቶች የማን ስም ሊጠራ ነው? ማን ሊሸለም ነው? የሚለው አባባል ትናንትና እንዳንቀሳቀስ በሰንሰለትና በገመድ እጅ እግሮቻችንን ብቻ ሳይሆን አዕምሮአችንንና አስተሳሰባችንንም ጭምር አስሮ የያዘን ትብታብ ነው። ከዚህ ትብታብ መላቀቅ የግድ ይለናል። ያንን መሰናክል ሰብረን ካልወጣን እመኑን አሁንም እንደ በሬ ሽንት ወደኋላ እንጂ ወደፊት አንሄድም። ዕድገታችን አዝጋሚ እንጂ ፈጣን አይሆንም። ምናልባት ወደላይ በማደግ ፈንታ እንደ ካሮት ወደ ውስጥ እንዳናድግም እንሰጋለን።

እስካሁን ዞናችንን በመሩና ባስተዳደሩ አመራሮች ላይ ሆነ፣ ደረሰ፣ ተወራ፣ ተፈጸመ ከሚባሉ ክስተቶች፣ ሂደቶችና ተግባሮች እራሳችንን አጽድተን እንዴት ነው ለእውነት የምንቆመው? እስከ መቼ ነው በማህበረሰባችንንና በአካባቢያችን ጉዳይ ላይ ሚዛን ያጣና ምንጩ የማይደርቅና የማይነጥፍ አሉባልታ በሕዝቡና ሕዝቡን ሊያገለግሉ በቀረቡና በሚቀርቡ ግለሰቦች ዙሪያ በተለይ ምርጫው ሲቃረብ ወይም ሲደርስ የሚናፈሰው? እነዚህ ግለሰቦች ከዬት መጥተው ነበር ሲያገለግሉን የነበሩት? በኃላፊነት ቦታቸውና በበትረ ሥልጣናቸው እንዴት ነበር ሕዝቡን ሲያገለግሉ የነበሩት?

ለምንድን ነው ሕዝቡ የራሱን ልጅ (ሰው) “ቀን በበቁሎ ማታ በቆሎ” የሚያደርገው ወይም የሚለው? የራሳችንን ሰው እንዳናከብር፣ እንዳናሳድግ፣ እንዳንመክር፣ እንዳንወቅስ፣ እንዳንገስጽ፣ የጎበጣውን እንዳናቃና የሚከለክለን ምንድን ነው? ወገኔ! የማንን ጥሩምባ ነው እየነፋን ያለነው? እውነት ዛሬ እየዘራን ያለነው ዘር ነገ ለምናጭደው አዝመራ መልካም ቡቃያ ሊሆን ይችል ይሁን? ምርቱ ወይም ውጤቱ ለእኛነታችን ይመጥን፣ ይወክለን ይሁን? ወይስ የምንኖረውና የምንሰራው ሌላውን ለማሳደግና ለማፋፋት ነው?

በዞናችን የሚጎለው አንድነትና ትብብር ነውና አሁንም አሁንም ይታሰብበት! እኛና እናንተ ትናንትና በለፉትና በደከሙት ወንድም እህቶቻችን ላይ ያደረስነውን ጫናና በደል ዛሬም ሆነ ነገ በሚመሩ ወንድም እህቶቻችን ላይ በግፍ ላለማድረስ የምንሰጠው ዋስትና ይኖረን ይሁን? ወይስ አሁንም ቀድሞ የተዘራብንን እንክርዳድ፣ እሾህና አሜኬላው እንዲበቅልብን ነው ዕድል ፈንታ እየሰጠን ያለነው?

በከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም ፌስቡክ ገጻችን ላይ የሰፈረው “ኅብረተሰባችንንና አመራሩን” የሚመለከት ቢሆንም ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለማኅበረሰባችንና ለአካባቢው ካለንና ከምናደርገው እንቅስቃሴ፣ ዓላማና ግብ አንፃር ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው አንኳር ጉዳይ ስለሆነ ከግለኝነትና ከእኔት ወጥተን ለእኛ በሚለው መርኅና መፈክር ሥር ራሳችንን እንድናገኝና እንድናሰባስብ ለማሳሰብ ነው። እኛ እርስ በርስ በተበላላንና በተሻኮትን ቁጥር ቅሬታ በመኻከላችን እየገባና እየሰፋ፣ለራሳችን አመራሮች አላስፈላጊ ስያሜ እየሰጠንና እያሰጠን፣ አንዳችን ሌላኛችንን በክፉ ዓይን እያየንና እየተጎዳዳን ነው።

ይህንን አስጠሊታ የጥርጣሬና የብዥታ አባዜ አምጥተው ጭነውብን እስከዛሬ ድረስ እየተባላን እምነትና ስምምነት አጥተን እንድንኖር አድርገውን ለዚህ ሁሉ ችግርና መቃቃር ያበቃን ወያኔ ስለሆነ ከእንግዲህ መንቃት ይኖርብናል። አለበለዚያ እንደተኛን ሌሎች ጥለውን መሄዱ ብቻ ሳይሆን ጥቅማችንንም እያሳጡን ስልቱን እየተጠቀሙ ጫናቸውን እንዳያሳርፉብን እንሰጋለን።

ስለሆነም ችግሮቻችንን በነቂስ አውቀንና ደርሰን ከሥሩ ነቅለን በመጣልና በማስወገድ ለዕድገታችንና ለስኬቶቻችን አብረን እንደ አንድ ማኅበረሰብ መመካከር፣ መወያየት፣ መደማመጥና ለጋራ ውሳኔ መድረስና መቆም የሚጠበቅብን አሁን ነው። ሕዝባችንና መሪው ክፍል ቆም ብሎ በቀናነት ማወቅና ማሳብ ያለበት አንድ ትልቅ ቁምነገር የጋራ መድረክን መፍጠርና ከምንም በላይ ለአንድነታችንና ለጋራ ጥቅማችን በማያወላውል አቋም መቆም ነው! እንደ ዓይን ትንሽ እየበቃን አንዳችን በአንዳችን ላይ እየዶለትን ግፍና በደል እየሰራን የደረሰበት ክፍልም ሆነ ግለሰብ መክፈል የሌለበትን ዋጋና መስዋዕት እንዲከፍል ማድረግ አግባብ አይደለም።

በዘር፣ በጎሣ፣ በአምቻና በጋብቻ በተለይም ለዕድገት ማናቆ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተሸብበንና ታጥረን የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ወይም እርምጃዎች አሁን ላለንበት ዘመን አይጠቅሙንምና እባካችሁ ዓይናችንን፣ ግንዛቤአችንንና ልቦናችንን በእውነት በቀናነት ለጋራ ልማትና ዕድገት እናንሳ፤ እንስራ! የተከበረው ማኅበረሰባችን የቀደመውን ወይም የጥንቱን አንድነትና የጋራ እሴቶቹን እንዲመልስና በሚጠቅሙትና በሚያቀራርቡት ማኅበረዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባሮች ላይ አትኩሮ እንዲሰራ እናበረታታ! ከምንም በላይ የሚጠቅመን ኅብረት ነው፤ አንድ እንሁን!

ከሞላ ጎደል ከላይ በዝርዝር ለማስቀመጥ እንደተሞከረው እኛው በእኛው እየተጠላለፍንና እየተወነጃጀልን ከበሬታና አንቱታ እንኳን ለሚገባቸው መሪዎቻችን በአግባቡ አንሰጥም። አንዱን ጭንቅላታችን ላይ እያስቀመጥን ሌላውን ረግጠን የምንቆምበት አንዳች ምክንያት ሊኖር አይችልም። ሁሉም የእኛ ናቸው፤ በእኩል ዓይን ነው መታየትም ሆነ ማየት ያለብን።

በሌላ መልኩ የእኛውን እያጥላላን የሌላውን ማክበር፣ መካብና ማንገስ ትዝብት ውስጥ የሚጥለን አቀራረብ ነውና እንጠንቀቅ! “ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ” መሆን እጅግ ያሳዝናል፣ ያስተዛዝባልም።

እዚህ ላይ እንዳትሳሳቱ! እያልን ያለነው ክብር ለሚገባው ክብር፣ ምስጋና ለሚገባው ምስጋና፣ ወቀሳ ለሚያስፈልገው ወቀሳ አስፈላጊና ተገቢ ነው። ግን የጅምላ ፍርጃ ከቅናትና ተንኮል በመነሳት የሚደረገው ጠልፎ መጣልና በቀል በፍጹም ከምድራችንና ከማኅበረሳብችን መካከልና አዕምሮ መወገድ ይኖርበታል።

እስቲ ሁላችንም ቆም ብለን ራሳችንን እንፈትሽ! እኛን ከሌላው ማህበረሰብና አካባቢ በተለየ ሁኔታ እንዳያድግና ለውጥ እንዳያመጣ ያደረገው አንድ ቋንቋ መናገራችን ነው ወይንስ አንድ ሆነን አለመገኘታችን ነው?

ይኼ ግለኝነት፣ እኔነትና ጠባብነት ከዬት መጣ? ስንቶቻችን ነን በቤተሰብ፣ በሰፈር፣ በመንደር፣ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በልዩ ወረዳ፣ በክልል ተብዬውና በሀገር ደረጃ እያስተናገድን ያለነው? ትርፉንና ኪሳራውን አመዛዝነን አውቀናል? አንድ ሁሌ የሚገርመን ነገር፥ ራሳችንን በየጊዜው እየገደልንና እየቀበርን ማን እንዲያነሳን ነው የምንፈልገው ወይም የምንጠብቀው? እስከ መቼስ ነው እየተባለንና እየተሻኮትን የምንኖረው? እንዴት አንተ ተው፣ አንቺ ተዪ የሚል ሽማግሌ ወይም ምሁር ከማህበረሰባችን ይጥፋ!? እጅግ ወደሚያሳዝን የዕድገት አቅጣጫስ ለምንድን ነው የምናዘቀዝቀው?

ወደድንም ጠላንም አሁን የሚያሻን ሁላችንም ሁለተናችንን ለጋራ አንድነት፣ ዕድገት፣ ስኬትና ውጤት መስጠት ነው! ቡድን ወይም ጎራ ፈጥረን መባላት፣ መናቆር፣ “የX ወይም የY” ነኝ ወይም ነህ መባባሉና ማስባሉ ይቁም፣ ይወገድ! አልጠቀመንም፣ አይጠቅመንም፣ ልጥቅመንም አይችልም!

አሁን በፈሰሰው ወተት ላይ ማልቀስ ዋጋ የለውም። በርግጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስካሁን በሕዝባችን፣ በአመራሩና በአካባቢው ዕድገት ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለደረሰው ስልታዊ ጥቃት እናዝናለን፤ እንቆጫለን። ይህ ሕዝቡንም ሆነ የለፋውን አመራር (ወገን) የማይጠቅም በመሆኑ ከምባቶማ አክሽን ዓለም አቀፍ ፎረም በኅብረተሰቡ መካከል ህብረትና መከባበር ይበልጥ እንዲጎለብት፣ ጥላቻና መጠላለፍ እንዲወገድ፣ ማንኛውም ለዕድገትና ለመለወጥ እንዲሁም ለመተባበር አዳጋች በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚችለው አቅም በርትቶ ይሰራል። በሕዝቡና በአመራሩ መካከል የጠበቀ ግንኙነትና ተዓማምነት ቢኖር ውጤቱ ያማረ ስለሚሆን እርምጃችን ለአንድነትና ለጋራ ስኬት ይሁን እንላለን!

ኡጀቀንቹኔ ምናደብሃት! ሜጦመት መቆሃ! ሰላም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ይሁን!

1 view0 comments

Comments


Post: Blog2_Post
bottom of page