top of page
Search

ከከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም የተሰጠ መግለጫ

Writer's picture: kambattomaikambattomai

አድሎአዊነትና ኢፍትሃዊነት የሕብረብሄራዊነትና የብልጽግና ጸር ናቸው። የቀድሞው የደቡብ ክልል መፍረሱን ተከትሎ ሁለት አዳዲስ ክልሎች ማለትም የደቡብ ክልልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል መዋቅር አደረጃጀት ሂደት ለከምባታ ጠምባሮ ዞን አንድ መሥሪያ ቤት ብቻ እንደተመደበ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም ጉዳዩን በቅርበት በመከታተልና ከሕዝባችን የተለያዩ አካላት ጋር በመመካከር ላይ ይገኛል። ለአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖችና ልዩ ወረዳ ከተመደቡት 32 ቢሮዎች (መሥሪያ ቤቶች) መካከል አንድ የግብርና ቢሮ ብቻ ለሰፊው የከምባታ ጠምባሮ ዞን መመደቡ በማንኛውም መለኪያና መስፈርት ተቀባይነት የሌለው አድሎአዊና ኢፍትሃዊ አሰራር በመሆኑ የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም በጽኑ ይቃወማል። አንድን ሕዝብ በጅምላ የሚበድልና የሚቀጣ ውሳኔ አዘጋጅተው ያቀረቡ፤ ውሳኔውን ያስተላለፉ፤ ያጸደቁና ለትግበራ ያቀረቡ የክልል ባለሥልጣኖች ሁሉንም ሕዝቦች በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለማገልገል የተጠለባቸውን መንግስታዊና ህጋዊ አደራን የዘነጉ መሆናቸውንም በዚህ አጋጣሚ ለማስገንዘብ እንወዳለን። ዛሬ በቢሮዎች ምደባ የተገለጠው ግልጽ አድሎአዊነት በከምባታ ጠምባሮ ዞን ሕዝብ ላይ የደቡብ ክልልን ለ27 አመታት ሲመሩ በነበሩ የደህዴን ባለሥልጣኖች መሪነት ሲተገበር መቆየቱን ሁሉም የሚያውቀው የአደባባይ ምስጢር ነው። የአሁኑ የተዛባ ውሳኔ በቀደሙት አመታት አንዳንዶቹ የደህዴን መሪዎች ለከምባታ ጠምባሮ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት በሚዲያ ጭምር ወጥተው በአደባባይ ሲናገሩ ከነበረው አሳፋሪ ሌጋሲ የመነጨ እንደሆነም ድርጅታችን ይገነዘባል። የኢህአዴግ መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ለብዙ ዘመናት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የልማት፤ የትምህርትና የጤና ተቋሞች በመሰማራት በቀዳሚነቱ የሚታወቀውን ታታሪውንና ሥራ ሕይወቱ የሆነውን የከምባታ ጠምባሮ ሕዝብ ”የመልማት ፍላጎት የሌላቸውና የልመና እጆቻቸውን የሚዘረጉ” ናቸው በማለት እጅግ አሳፋሪና መሰረተቢስ መግለጫ በትዕብት ከተናገሩት ቀደምት የዴህዲን መሪዎች እግር የተተኩ የብልጽግና ፓርቲ የክልል አመራሮች የቀደመውን በደል በተለያየ መልኩ ሲያስቀጥሉ ቆይተዋል። ሌላው ቀርቶ በጀት ተይዞላቸውና ጸድቀው ለዞኑ የመጡ ፕሮጀክቶች የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው ለዞኑ ማህበረሰብ ዜና መሆን ካቆመ ሰንብቷል። ከ32 ቢሮዎች ውስት 56 ፔርሰንቱን በሁለት ዞኖች ብቻ ጠቅልሎ አንዲቷን ብቻ ለከምባታ ጠምባሮ ዞን ለመስጠት የተደረገው ውሳኔ የነባሩ ኢፍትሃዊና አድሎአዊ አሰራር ተቀፅላ ነው ብለን ለማመን ያስገድደናል። ይህ ውሳኔ የብልጽግና ፓርቲና መንግሥት ምሶሶ የሆነውን የመደመር መርህ በቀጥታ የሚጻረር እና የጋራ ልማትና እድገትን በጋራ የማሳለጥ አቅጣጫን ያልተከተለ አግላይ አሰራር መሆኑ ታውቆ፣ ተገቢው እርምት እንዲደረግና የከምባታ ጠምባሮ ሕዝብ ከማንም ያላነሰና ከማንም ያልበለጠ ድርሻውን እንዲያገኝ፤ እንዲሁም ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር እኩል የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል የመንግሥት አካላት ክትትል አድርገው ተገቢውን ድርሻ እንዲያገኝ እንዲደረግ የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም አበክሮ ያሳስባል። ሥር ሰድዶ የኖረዉ የከምባታ ጠምባሮ ሕዝብን አሳንሶ የማየት መጥፎ አባዜ አክትሞ፤ በአዲሱ ክልል ሁሉም በሰላም፤ በፍቅር፤ በመተሳሰብና በእኩልነት የሚታይበት ፍትሃዊነትንና ሕብረብሄራዊነትን ያማከለ አሰራር እንደሚዘረጋ ተስፋችን የጎላ ነው። በመጨረሻም የከምባታ ጠምባሮ ሕዝብ ተወካዮች፤ ሽማግሌዎች፤ ምሁራን፤ አክቲቪስቶችና አመራሮች ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ በአንድ ሃሳብና በአንድ ልብ ለመስራት ያሳዩትን ተነሳሽነት፤ ትጋት፤ ሕብረትና ቁጭት ድርጅታችን በእጅጉ እያደነቀ፤ ይህን የአንድነት ስሜትና መነሳሳት ይበልጥ በማሳደግ ሕዝባችንን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረጉት ጥረቶች ሁሉ የከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም አቅሙ በፈቀደው መጠን አብሮ የሚሰለፍ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። ፍትህ ለከምባታ ጠምባሮ ሕዝብ። ሰላምና ብልጽግና ለኢትዮጵያ። ከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም። ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ኦገስት 11, 2023


2 views0 comments

Comments


Post: Blog2_Post
bottom of page