ለከምባታ ጠምባሮ ዞን መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት
ዱራሜ
በቅርቡ ወደ አረብ ሀገሮች ለሥራ እንዲሄዱ በከምባታ ጠምባሮ ዞን በተመለመሉ ወጣቶች ላይ ተከሰተ ተብሎ በማስሚዲያ እየተናፈሰ ያለው ወሬ ማህረሰባችንን የሚጎዳ ሆኖ ይሰማናል። እንደሚወራውና እንደሚነበበው ከሆነ የአጎራባች ዞን ተወላጆች በከጠ ዞን ኮታ እንዲገቡ ተደርገዋል። እውነት መሆን አለመሆኑን ባናውቅም፤ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ተቆርቋሪ የዞኑ ተወላጆችና የድርጅታችን አባላት ስለጉዳዩ እየጠየቁን ይገኛሉ። ከዚህም የተነሳ እኛም የጉዳዩን አሳሳቢነት በማየትና የሚናፈሰውን ወሬ ለማጣራት በማሰብ የሚመለከተዉን የዞኑን አስተዳደር ክፍል ለመድረስና ለማነጋገር ተከታታይ ጥረቶችን ብናደርግም እስክሁን ድረስ ጥረታችን ሊሳካልን አልቻለም።
በአሁኑ ወቅት ባለው ሀገራዊና አካባቢያዊ ውስብስብ ሁኔታዎች የተነሳ በዞኑ ትምህርታቸውን ጨርሰው የተቀመጡ ሥራአጥ ወጣቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሆኖ ሳለ፣ ይባስ ብሎ የመጣላቸውን እድል ለመጠቀም እንዳይችሉ መደረጉ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ ሁላችንም እንገነዘባለን።
እዚህ ላይ ሊተኮር የሚገባው ጉዳይ ሁላችንም ለአካባቢያችንና ለህብረተሰባችን መልካም እንዲሆን የምናደርገው ጥረት ሕጋዊ ባልሆነ አካሄድና አተገባበር የማህበረሰባችንን ዕድል የሚያጨናግፍ ሁኔታ መፈጠር የሌለበት መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ የዞኑም ከዞኑ ውጭ የሚገኙ ተወላጆች እምነት እንደሆነ እናምናለን።
ስለሆነም የዞኑን አስተዳደርና የሚመለከተውን ክፍል የምንጠይቀዉ ጉዳይ ቢኖር እየተወራ ያለው ጉዳይ እውነት በዞናችን ሥራ ፈላጊዎች ላይ ተፈጽሟል ወይ? የሚለዉን ጥያቄ ነው። ካልተፈጸመ የሚናፈሰውን ወሬ በትክክለኛ መንገድ ማስቆም የዞኑ አስተዳደርና አመራር ሃላፊነት ነው ብለን እናምናለን። ስለዚህ ደረሰ የተባለውን ድርጊት በማጣራትና በማሳወቅ ረገድ የዞኑ አስተዳደር የተወራው ጉዳይ ሐሰት ወይም እውነት መሆኑን ከተወሰደው ወይም ከሚወሰደው እርምጃ ጋር ለመላው የዞኑ ሕዝብ ቢያሳውቅ መልካም መሆኑን እንጠቁማለን። ይህን የምንጠይቅበትም ምክንያት ማህበረሰባችን ተፈጠረ ለተባለው ጉዳይ መልስ አግኝቶ አንድነታችንን አጠናክረን አብረን ለመጓዝ እንድንችል ስለምረዳን ጭምር ነው።
ከምባቶማ አክሽን ኢንተርናሽናል ፎረም። መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም.
ግልባጭ፡ ለከምባታ ጠምባሮ ዞን የብልጽና ጽ/ቤት
Email: kambattomai@gmail.com; twitter: @kambattoma; Facebook: Kembattoma Action International Forum | Rockville MD | Facebook; WhatsApp: Kambattoma International; Website: https://kambattomai.wixsite.com/
Comments